ከሚያዝያ 10/ 2018 ዓ.ም አንስቶ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አማካይነት የተለያዩ ምስሎች “የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)ን አዲስ ሙዚቃ ያዳመጡ ወጣቶች መታሰራቸውን” ከተለያዩ ምስሎች ጋር ሲያጋሩ ተስተውሏል፡፡
ትርታ ቼክም የምስሎቹን እውነታነት ላይ ምርመራ አካሂዷል፡፡

ከሚያዝያ 10/ 2018 ዓ.ም አንስቶ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በተለይም በፌስቡክ እና በትዊተር ላይ “105 ወጣቶች የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)ን አዲስ ሙዚቃስላዳመጡ መታሰራቸውን”ከሁለት ምስሎችን ጋር በማያያዝ ሊያጋሩ ተመልክተናል፡፡

ከነዚህም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መካከል ስንታየው ቸኮል በተባለና ከ106 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት ገፅ መረጃውን ከምስል ጋር አጋርቶታል፡፡ ይህ ልጥፍ “አብዮቱ ተጀምሯል” በሚል ርዕስ ዝርዝር መረጃ ከምስል ጋር የያዘ ሲሆን ፤ ምስሉም “ የጸጥታ አካላት ወጣቶችን በቁጥጥር ስር አውለው” ያሳያል፡፡ ይህ ከ2ሺህ በላይ ሰዎች ላይክ ያደረጉትና ከ 150 በላይ ሰዎች ያጋሩት መረጃ ከሰዓታት በኃላ ፎቶው ተቀይሯል፡፡

በተመሳሳይ ተስፋ ኒውስ የተሰኘና ከ 40 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት እንዲሁም ፒያሳ ቲዩብ የተሰኙ የትዊተር ገጾች መረጃውን ከሌላ ምስል ጋር አጋርተውት ተመልክተናል፡፡

በመሆኑም ትርታ ቼክ የሁለቱንም ምስሎች ከተጠቀሰው መረጃ ጋር ያላቸውን ትይይዝ መርምሯል፡፡

የጎግል ምስል ማፋለጊያ መሳሪያን በመጠቀም ባደረኘው ፍለጋ ይህ ምስል ቢያንስ ከመስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ ማላትም ላለፉት 7 ዓመታት በኢንተርኔት ላይ የነበረና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏ፡፡ (ለምሳሌም ይህንን ፣ ይህንንና ይህንን ሊንክ ይመልከቱ) በመሆኑም ይህ ምስል በመረጃዎቹ ላይ እየተጠቀሰ እንደሚገኘው አሁን ካለ ክስተት ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ይህንንም ምስል በጎግል መረጃ አፋላጊ የመረመርን ሲሆን በውጤቱም ይህ ምስል በኢንተርኔት ላይ የቀናት እድሜ ብቻ ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ምርመራችንንም በመቀጠል ፤ ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት AI መሰራት አለመሰራቱን AI or Not በተባለ የዲጂታል መሳሪያ ተጠቅመናል፡፡ ውጤቱም እንደሚያሳየው ምስሉ በ AI የተፈጠረ እንጂ እውነተኛ ክስተትን የሚያሳይ አይደለም።

ይሁን እንጂ ከምስሎቹ ባሻገር ፤ የተጠቀሰው መረጃ ማለትም በርካታ ወጣቶች መታሰራቸውንና ምክንያቱም ‘የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ዘፈን መውጣቱን ተከትሎ” መሆኑን የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የዘገቡ ሲሆን መንግስት በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹን የያዛቸው “ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈፀም ታጥቀው በጫካ ከሚንቀሳቀሱ የሽብር እና ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የኢትዮጵያን ሰላም እና ደኅንነት ለማወክ እንዲሁም መጪውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ ስምሪት ወስደው ሲንቀሳቀሱ” ስለነበር መሆኑን በመንግስት ሚዲያዎች በኩል አስታውቋል፡፡ ትርታ ቼክም “የታሰሩ ሰዎች ስለመኖር አለመኖራቸው” የቤተሰብ አባላቸው በተለምዶ 3ተኛ በሚባለው የፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩባቸው ከእማኞች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
በመሆኑም ቁጥራቸው 138 የሚደርሱ የታሰሩ ቢሆንም ፤ መረጃዎቹ ሲሰራጩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ያጋሯቸው ምስሎች ግን የቆዩና የሰሞኑን ሁነት የማያሳዩ እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተፈጠሩ መሆናቸውን ትርታ ቼክ አረጋግጧል። ስለሆነም የታሰሩ ሰዎች መኖራቸው ትክክለኛ መረጃ ሲሆን ተያይዘው የተሰራጩት ምስሎች ግን ሀሰተኛ በመሆናቸው መረጃው ትርታ ቼክ አረጋግጧል፡፡
“ኤሪ ብሉምበርግ” የተሰኘ የኤክስ (ትዊተር) አካውንት አንድ የ19 ሰከንድ ቪዲዮ ክሊፕ “PP is pumping more security toward Addis Abeba after the release of ”Tedy Afro’s album” ከሚል ጽሑፍ ጋር አጋርቶ ተመልክተናል፡፡ ይህ አካውንት ቪዲዮውን ያጋራው “የድምጻዊ ቴዲ አፍሮን አልበም መለቀቅ ተከትሎ ብልጽግና በርካታ የጸጥታ አካላትን እያሰማራ መሆኑን በመጥቀስ ሲሆን በቪዲዮውም ላይ ወጣቶች በግርግር በዋና መንገድ ላይ ሲሯሯጡ ይታያል፡፡
ትርታ ቼክም የዚህን መረጃ እውነተኝነት አጣርቷል፡፡

ትርታ ቼክ መረጃውን ለማጣራትም የ ኢንቪድ ዊ ቬሪፋይ መሳሪያ የተጠቀመ ሲሆን ይህም መሳሪያ የቪዲዮውን ቁልፍ ማእቀፎች (ፍሬሞችን) ስክሪንሹት በመውሰድ ቪዲዮው ከዚህ በፊት በኢንተርኔት ላይ የተለቀቀ መሆን አለመሆንኑ ያሳየን ሲሆን ፤ በውጤቱም ይህ ቪዲዮ ከአምስት አመታት በፊት በAFP አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዩቲዩብ ገጽ ላይ ተለቆ የነበረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመሆኑም ይህ የ19 ሰከንድ ቪዲዮ ከአምስት ዓመታት በፊት አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ላይ በተፈጸመው ግድያ ምክንያት ስለፈኞች ለተቃውሞ ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውንና በጎዳናዎች ላይ በብዛት መታየታቸውን ከሚዘግበው የAFP የ 56 ሰከንድ ቪዲዮ ላይ የቆርጦ እንደአዲስ የቀረበ አሳሳች መረጃ ነው፡፡ በትዊተር ላይ እንደተዘገበውም ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የሚያያይዘው ነገር ባለመኖሩ ትርታ ቼክ መረጃውን ሀሰት ሲል በይኖታል፡፡