ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም “ዲጂታል ኢትዮጵያ” በተሰኘና ከ36 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት ገፅ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትግራይ ክልል ቁልፍ ቦታዎች ላይ የድሮን ቅኝት ማድረጉን የሚገልጽ “ሰበር ዜና” በምስል ታጅቦ ሲሰራጭ ተመልክተናል። ልጥፉ የአየር ኃይሉ የህወሓትና የሻዕብያ የጦር ካምፖችንና መደበቂያዎችን መቃኘቱን የሚገልጽ ሲሆን፣ እስካሁን ከ1,100 በላይ ‘Like’ እና ከ50 በላይ ‘Share’ ተደርጓል።


ትርታ ቼክ የመረጃውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ምስሉን በዲጂታል የማጣሪያ ዘዴዎች የመረመረ ሲሆን በጎግል ሌንስ ባደረግነው የገጽታ ፍለጋ ማጣራት፣ ምስሉ አሁን በትግራይ ክልል የተነሳ ሳይሆን በፈረንጆቹ May 9, 2025 caspianpost.com በተባለ ዓለም አቀፍ የዜና ድረ–ገጽ ላይ የወጣ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። በምስሉ ላይ የሚታየው ድሮን የቱርክ ምርት የሆነው Bayraktar Akıncı ሲሆን፣ በሁለተኛው ምስል ላይ በድሮኑ ጭራ ላይ የቱርክ ባንዲራ ምልክት በግልጽ ይታያል። ይህም ምስሉ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ወቅታዊ እንቅስቃሴ ጋር የማይገናኝና ከሌላ የውጭ ሀገር ምንጭ የተወሰደ መሆኑን ያሳያል።
በትግራይ ክልል የድሮን ቅኝት ተደረገ በሚል በ“ዲጂታል ኢትዮጵያ” ገፅ የተሰራጨው ምስል የቆየና ከሌላ ዓለም አቀፍ ድረ–ገጽ የተወሰደ በመሆኑ፣ የቀረበው መረጃ መሠረተ ቢስ መሆኑን ትርታ ቼክ አረጋግጧል ።